በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር“የሃገራችን የሚድያ ተቋማትና የሚሰጡት አገልግሎት በህዝብ እይታ”! በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ተገኝተው ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት፡

ክቡር ዶ/ር ጌታቸዉ ድንቁ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የተከበራቹሁ፣ የመንግስትና የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች ፣ ከተለያዩ ሚድያ ተቋማት በመወክል የዚሀ መድረክ አካል የሆናችሁ ሃላፊዎችና ባለሞያዎች፣ ከተለያዩ የእምነት ተቋማት የተወከላቹሁ የሃይማኖት አባቶች፣ የተፎካካሪ ፖርቲ አመራሮች፣ የሞያና ስቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ በክልላችን ከሚገኙት ዩኒቨርስቲዎች የታደማችሁ ሙሁራን በአጠቃላይ የዚህ መድረኽ ተሳታፊዎች

ክቡራትና ክቡራን

በቅድምያ “የሃገራችን የሚድያ ተቋማትና የሚሰጡት አገልግሎት በህዝብ እይታ”! በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ለመሳተፍ እንኳን በድህና መጣችሁ ለማለት እፈልጋለሁ።
ይህ ወቅታዊ የሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከሚድያ አውታሮች የአገልግሎት አሰጣጥና ለህዝብ ያላቸዉን ዉግንናም ሆነ ተደራሽነት ምን እንድሚመስል ለመፈተሽና ለመዳሰስ የሚያስችለንን መድረክ እንዲዘጋጅና የዉይይት መድረኩ በዚህ መልኩ እንዲመቻች ላደረጉት የኢትዮጽያ ብሮድካስት ባለስልጣንና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በራሴና በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ስም ለማመስገን እወዳለሁ።
የዚህ መድረክ ዋነኛ አላማ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት የሚድያ ፕሮግራም ግድፈቶችን እንዲታረሙ በማድረግ ሚድያው የህብረተሰቡ ፍላጎት እንዲሁም መብትና ጥቅምን በማረጋገጥ ለሃገር ሰላምና እድገት ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑንና አለመሆኑን ለመዳሰስ፣ በማያይዝም አገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በዝርዝር ለማየት ብሎም ገንቢ ምክረ ሃሳቦችን በመለገስ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ጭምር የምናስቀምጥበት ይሆናል።

ክብራትና ክቡራን

እንደሚታወቀው ባለፉት 28 አመታት በተለይም ደግሞ ከዛሬ 3 አመታት በፊት በነበሩት ግዝያት መንግስታችን በልማታዊና ዲሞክራስያዊ መስመር እየተመራ በሰላም፣ በልማት ፣ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታና፣ በመልካም አስተዳደር ረገድ አንፀባራቂ ድሎችን ስያስመዘግብ የሚድያ ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ እንደነበረ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም።

በተጨማሪም የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ህገ‐መንግስትና ህብረ‐ብሄራዊ ፊዴራለዊ ስርአቱ ያጎናፃፋቸዉን መብቶች በመጠቀም የልማቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ፣ ራሳቸዉ በራሳቸዉ እንድያስትዳድሩ፣ በቋንቋቸዉ እንዲማሩና እንዲዳኙ ፣ በባህላቸዉና በማንነታቸዉ እንዲኮሩ፣ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች በጋራና በአብሮነት ተካባብርዉና ተቻችልዉ የመኖር እሴት እንድያጎለብቱና በማንነታቸዉ ሳይሸማቀቁ በኢትዮጽያዉነታቸዉ እንዲኮሩ ከፈተኛ ስራ ተሰርተዋል።

በዚህ ሂደት የሚድያዎች አስተዋፅኦም በዝያዉ ልክ ገንቢ እንደነበረ ሁላችንም የምናስታዉሰዉ ሃቅ ነዉ። ለዚህም ነበር በዚች አገር ከጫፍ ጫፍ የተረጋጋ ሰላም ሰፍኖ የነበረዉ፣ ዜጎች በመረጡት አካባቢ በሰላም ሰርተዉ ሃብትና ንብረት አፍርተዉ የመኖር መብታቸዉ ተከብሮ የነበረዉ፣ ይህቺ አገር ከቁልቁለት ጉዞና ከአስከፊ የድህነት አረንቋ ወጥታ በእድገት ጎዳና ግስጋሴዋን በማጠናከር የነበራት ገፅታ ተቀይሮ አለም የመሰከረለትን የፈጣን ልማት ተምሳሌት ለመሆን በቅታ የነበረዉ።

ይሁን እንጂ ካለፊት 3 አመታት ወዲህ በተለይ ደግሞ ከዛሬ አንደ አመት ተኩል ገደማ የልማታዊ ዲሞክራስያዊ ስርአት መርሆና አስተሳሰብ እየተሸረሸረ በመምጣቱ ምክንያት፣ አገራችን የጀመረችዉን የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራስያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት እንዲደናቀፍ ከመደረጉም ባሻገር ሩቅ አዳሪዉ የህዳስያችን ጉዞና ራእይ አቅጫዉን ስቶ ለህዝብ ተቆርቃሪ በመምሰል ቀን ከለሊት ሃገርን ለማፍረስ በሚኳቱኑ ህዝበኛ የትምክህት ቡድን እጅ ሊወድቅ በመቻሉ በህዝቦች መካከል መቃቃርን፣ ጥላቻን፣ ብሄር መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችና መፈናቀሎች፣ ዜጉች ላባቸዉ አንጠፍጥፈዉ ያፈሩት ሃብትና ንብረታቸዉ በጠራራ ፀሃይ እንዲዘረፍና ያለምንም ካሳ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ የተደረገበት፣ ህዝቦች በማንነታቸዉ ሲጨፈጨፉ፣ ሲታረዱ፣ የጋራ አዉራ መንገዶች ለአመታት በጎበዝ አለቆች ሲዘጉ ሃይ ባይ መጥፋቱና፣ በሚድያዎችም ጭምር በመንግስት አመራሮች ሳይቀር ህዝብ እንድ ህዝብ ተለይቶ መቀጣት ስላለበት ነዉ ተብሎ ሲነገር ነዉር ነዉ ባይ በጠፋበት፣ አልፎ ተርፎም በአገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሰው ፍጡር ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰበውን በአደባባይ ሰው ሰቅሎ እስከ መግደል የተደረሰበት ዘመን ላይ ለመገኘታችን ክርክር ዉስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም።

የዚህ ዘመን አሳዛኝ ገፅታዉ ደግሞ ሚድያዎች በተለይ ንብረትነታቸዉ የመንግስትና የህዝብ እንደሆኑ የሚታወቁት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ከአገራችን ታሪክና ከህዝባችን ባህል ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲፈፀሙ፣ ሰምተዉ እንዳል ሰሙ፣ አይተዉ እንዳላዩ፣ ጀሮ ዳባ ልበስ ብለዉ ወይም ደግሞ ለማስመሰል ነካክተዉ ከማለፈቸዉ ባሻገር ህዝብን እንደ ህዝብ ወዳጅና ጠላት ብለዉ የለዩና በሃገሪቱ ህግና ስርአት የሌለ እስኪመስል ድረስ፣ ያንዱን ጥፋትና ስህተት ከማረም ይልቅ በመደበቅ በሌላ በኩል ያንዱን ብሄር እንደ ብሄር ለማጥፋት የቁጥር ስሌት ተሰልቶ የዘር ማጥፋት አዋጅ የታወጀበት (እንደ ኢሳት ሚድያ) ፣ በተመሳሳይ ብሄርን መሰረት ያደረገ እልቂት እንዲፈፀም የሚያበረታታ ዶክሞንታሪ ፊልም ተሰንዶ የፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላትን በመተካት ፍርድ እስከ መስጠት የደረሰ በአንድ ቀን፣ በተመሳሳይ ስአት፣ ለዝያዉም በመንግስት የጋራ ሚድያዎች (ኢቢሲ፣ ዋልታና፣ ፋና) የክተት አዋጅ የታወጀበትና አታሞ የተመታበት፣ አልፎ ተርፎም የተሰጣቸዉ የህዝብ ሃለፊነት ወደ ጉን በመተዉ የህዝብ ድምፅ በማፈን የተባለዉን እንዳልተባለ፣ ያልተባለዉን እንደተባለ በዉሸት መረጃ ህዝብን በማደናገር ስራ ላይ ተጠምደዉ ከርሟል።

አሁን ባለዉ ነባራዉ ሁኔታ የአገራችን ሚድያ የህዝብና መንግስት ተቋም መሆናቸዉን ቀርቶ የእንጨብጣችኋለን ፉኳራና ቀረርቶ ነጋሪት የሚጎሰምበት ተቋም በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። አሁንም የዚሁ ቅጥያ የሆነ ዝርዝር የቤት ስራ ተሰጥቶቸዉ በባለፈዉ የስህተት መንገድ ሲዳክሩና ተመሳሳይ ዘመቻ ለማካሄድ እየኳተኑ እንደሚገኙ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች እንዳሉን በመጠቆም፣ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ከእዉነታ የራቀ መረጃ ለህዝብ ማስተላለፍ ሄዶ ሄዶ፣ በህዝብ ዘንድ ያለቸዉን ተአማኒነት ጥያቄ ዉስጥ እንደገባ አዉቀዉ ከአፍራሽ ድርጊታቸዉን እንዲቆጠቡ እያሳሰብን። ህዝባችንም የህዝብ ፍላጎትና ድምፅ በማፈንና ወደ ጎን በመተዉ በበሬ ወለደና፣ እንቶ ፈንቶ አጅንዳዎች የተጠመዱ ሚድያዎችን በቃ ሊላቸዉ ይገባል። በአንፃሩ ለብሮድካስቱ አዋጅና ለሞያዉ ሰነ‐ምግባር ተገዢ በመሆን የአገርና ህዝብ ሃላፊነት ተሰምቷቸዉ ያለዉን የአገሪቱ ነባራዉ ሁኔታና እዉነታ መሰረት አድርገዉ ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ በማቅረብ ላይ የሚገኙት ሚድያዎች ግዜ ወደ ግዜ በህዝቦች ዘንድ ተደማጭነታቸውና ተአማኒነታቸው እያደገ መምጣቱን ተገንዝበው ትክክለኛ መረጃ ወደ ህዝብ የማድረሱን ስራ አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል።

ይህንን ስንል የብሮድካስት አዋጅ፣ የፕሬስ ነፃነት አዋጅ እንዲሁም መሰል ህጎችና የአሰራር ደንቦች መከበር ሲገበቸዉ ያለምንም ሃይ ባይነት ሚድያዎች ለህዝብ ሰላምና አብሮነት ሳይጨነቁ እነዳሻቸዉ ሲፈነጩና፣ በሰበብ አስባቡ የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች ተጥሰዉ፣ ሃገር በጉልበቶኞች ስትታመስ ሚድያዎች ለመሰረታዊ የህዝቦች ፍላጎትና ጥያቄ በብቁ መረጃና ትንታኔ አስደግፈዉ መልስ ከመስጠት ይልቅ ለትምክህት ቡድኑ መሳርያ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ በተለይ ከላይ የተጠቀሱት ሚድያዎች በዚች አገር እያጋጠሙ ለሚገኙት ችግሮች ሁሉ በህግም በታሪክም ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል።

በመጨረሻም የዛሬዉ መድረካችን ሚድያዎቻችን የህዝብ ፍላጉትንና የብሮድካስት ህጉን በማክበር ለሃገር ሰላም፣ ለህዝቦች በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትና አብሮነት መዳበር በጋራ እንዲቆምና ለዚሁ መርሆ ተገዢ እንዲሆኑ የሚያስችል በሳልና ጥልቅ ውይይት እንድናደርግ እያሳሰብኩ መልካም የውይይት ግዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

ክብርና ሞጎስ ለትግሉ ሰማእታት!

አመሰግናለሁ!

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መቐለ ፡ጥቅምት 17 2012 ዓ/ም

By admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Show Buttons
Hide Buttons