የዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ሙሉ መልእክት!

የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ 
የተከበራችሁ የመላ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ተሳታፊዎች፣
የተከበራችሁ የመቐለና አካባቢዋ ነዋሪዎችና ታዳሚ እንግዶች፣
ክቡራትና ክቡራን ፣
ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለ3ኛው መላ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር አደረሳችሁ አደረሰን እያልኩ፣ የስፖርት ውድድሩ የመክፈቻ መልእክት ለማስተላለፍ በመታደሜ የተሰማኝ ከፍተኛ ደስታ እየገለፅኩ፣ በራሴና በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስም የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት ወደ ሆነችው ሰሜናዊት ኮኮብ መቐለ ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባደረጉት መራራ ትግል የድህነት ዘብ የነበረውን አምባገነን ወታደራዊ ስርዓት በመገርሰስ፣ አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ መጠቀም የሚያስችላትን ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍ፣ ለሰብአዊ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት በአገራችን አዲስ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ምዕራፍ መከፈቱ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ 
በመሆኑም ሁሉም የአገራችን ህዝቦች እጅና ጓንት ሆነው ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጸረ ድህነት ትግል፣ ሁሉንም ህብረተሰብ በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገና ሁለንተናዊነትን የተላበሰና የዓለም ሕብረተሰብም የመሰከረለት ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ተመዝግቧል።
የለውጡ አንድ አንጓ የሆነው ስፖርትም ባለፉት 27 አመታት እያደገ መምጣቱ ይታመናል:: የአገራችን ስፖርት ምንም እንኳ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ባይቻልም ፣ በዓይነትና በአቅም ለውጥና እድገት እያሳየ መምጣቱ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡
እንሆ ዛሬ መጋቢት 14 የሚጀመረውና የሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድርም የዚሁ እድገት አንዱ አካል ነው።
እንደሚታወቀው ስፖርት ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው:: ጤናማ አእምሮ ያለው አምራች ዜጋን በማፍራት የአገርን ብልጽግና እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ዓላማውን ባግባቡ በመገንዘብና ጠንቅቆ በማወቅ ከተመራና የህብረተሰቡና የመላው የስፖርት ወዳጅ ማህበረሰብ ድጋፍ ከታከለበት በጤናማ አስተሳሰብ የተገነባና በሰናይ ስነምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ስፖርት ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ስፖርት ሰላምንና መረጋጋትን ለማስፈን የሚኖረው ጠቀሜታም በእጅጉ የላቀ ነው:: ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መክፈቻ ቁልፍ እንደሆነ ይታወቃል:: ሰላም ከሌለ ምንም ነገር አይኖርም:: በአሁኑ ወቅት የሰላም ጉዳይ ለአገራችን ትልቅ ፈተና ሆኖባታል፡፡ ዛሬ ይህን መሰል የስፖርት ውድድር ለማካሄድ የተዘጋጀው በክልላችን የተረጋጋ ሰላም ማስጠበቅ ስለተቻለ ነው።ስፖርት ይቅርና በተረጋጋ መንፈስ ለማካሄድ ማቀድ፣ዜጎች በሰላም ወጥተው የማይመለሱበት፤ ህዝቦች በከፍተኛ ደረጃ የሚፈናቀሉበት፣ ለበርካታ ጥቃቶችና ጉዳቶች የተጋለጡበት፣ ያልተረጋጋ ሁኔታ በአገራችን እንዳለ የሚታወቅ ነው። በመሆኑም የአገራችሁን ሰላም ለማረጋገጥ ሁላችሁም የድርሻችሁን መወጣት ይኖርባችኋል:: በትግራይ ክልል ያለው ሰላም የተገኘው በአጋጣሚ ሳይሆን፣ በክልላችን ህገ መንግስቱን በማክበር ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት፣ የሚሰሩበትና የሚኖርበት ሁኔታ አጠናክሮ በማስቀጠል ነው። 
ክቡራትና ክቡራን ፣
ወጣቱ ትውልድ በተለይ ደግሞ ተማሪዎችና ስፖርተኞች ከሁሉም በላይ የሰላም አምባሳደሮች ሊትሆኑ ይገባል፡፡ እናንት ወጣቶች የዛሬ ተማሪዎች የነገ ኢኮኖሚስቶች፣ መሃንዲሶች፣ ሃኪሞች፣ መምህራን፣ ፖለቲከኞች እና አገር መሪዎች የአገራችሁን ሰላም ለማረጋገጥ መትጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ተባብራችሁና አንድ ሆናችሁ ለሰላም መረባረብ ይጠበቅባቸኋል፡፡ 
የአገሪቱን ሕገመንግስትና ፌዴራላዊ ስርዓቱን በመናድ፣ የነበረውን የዴሞክራሲና የልማት ሂደት ለማሰናከል እንደዚሁም ተፈጥሮ የነበረውን የህዝቦች አንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት ለማክሰም በግልም ሆነ በቡድን እየተደረገ ያለውን ዘመቻ ጠንክራችሁ ልትታገሉት እና የደፈረሰው የአገራችንን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ በሚደረገው ትግል እናንተም የራሳችሁ ሚና ተጫወቱ።

የዛሬ ተማሪ ወጣቶች የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢ ሃይሎች በመሆናችሁ እርስ በርሳችሁ በመዋደድ፣ በመከባበር፣ ልዩነትን በማጥበብ፣ ከጥላቻና ከሚለያዩ ተግባራት በመራቅ፣ የሚያስተሳስሯችሁን እሴቶች በማጎልበት እና በማጠናከር ለብሩህ መጻኢ ድርሻችሁን መወጣት ይኖርባችኋል፡፡
የአገራችሁ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ባህልና የአኗኗር ዘይቤ በማወቅና በማክበር መልካም የግንኙነትና የትብብር መንፈስ በማሳደግ የበለጸገች አገር ለመገንባት የድርሻችሁን እንዲትወጡ አደራ እላለሁ፡፡ 
መቻቻልንና አብሮነትን እያጠናከራችሁ፣ ልዩነቶችንና ችግሮችን አግባብ ባለውና በሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየፈታችሁ፣ አንዱ ሌላውን ሳይንቅ ሌላው ሌላውን ሳይገፋ፣ በመከባበር፣ አንድነታችሁን በማጠናከር አገራችሁ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምትመች ሃገረ ሰላም፣ ሃገረ መከባበርና አብሮ ማደግ ትሆን ዘንድ ጥረት እንዲታደርጉ በዚህ አጋጣሚ ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡
ክቡራትና ክቡራን ፣
ዛሬ የሚጀመረው የመላ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር በመቐለ ከተማ መካሄዱ ወጣት ተማሪዎች ከውድድሩ ባሻገር የትግራይ ህዝብ ለሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለውን ፍቅርና እንግዳ አክባሪነቱን ለመገንዘብ ያስችላችኋል የሚል ሙሉ አመነት አለኝ፡፡ 
እዚህ አጠገባችን ያለው የሚታዩት ግዙፍ የሰማእታት ሀወልት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ስረግጥ የነበረውን የደርግ ወታደራዊ መንግስት ለመጣል በተደረገው የ17 አመታት መራራ ትግል የተሰዉ 60 ሺ የትግራይ ታጋዮችን ለማስታወስ የቆመ ሀወልት ነው። ለአገራችን ህገ መንግስትና ፌዴራላዊ ስርአት ለመመስረት በትግራይ ህዝብ የተከፈለው መስዋእትነት ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑ ማስታወሻ የሆነ የሰማእታት ሀውልት ነው።የትግራይ ህዝብ የቅርብና የሩቅ ታሪኩ፣ለአገሩ ከፍተኛ መስዋእት የከፈለ፣ ይቅርና የልዩ ጥቅም ተጠቃሚ ሊሆን፣የሚገባውም ያልወሰደ ህዝብ ነው።የትግራይ ህዝብ ለአገሩ ብሎ ስንት በደል ተሸክሞ፣ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኝ ህዝብ ነው። ይሁን እንጂ የወቅቱ ፖለቲከኞች ተብየ አይናቸውን በጨው አጥበው የትግራይ ህዝብ ያልሆነ የፈጠራ ታሪክና የሌለበትን ባህሪ ሊያላብሱትና ከሌሎች የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሊያለያዩት ቀን ተሌት ለሚዋትቱ ግለሰቦችና ቡድኖች የተዛባ መንገድ ለመምረጣቸው እናንተ ህያው ምስክር እንደሚትሆኑ አልጠራጠርም፡፡
የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተጋ ያለ ህዝብ ነው፡፡ በራሱ እንዲደርስበት የማይፈልገውን ነገር በሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ማድረስ የማይሻ ሰላም ወዳድ ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ሁሉም ሰላማዊ ህይወት እንዲመራ ይፈልጋል፡፡ ይህንን ለማሳካትም ጠንክሮ ይሰራል፡፡ ለዚህም ነው በትግራይ ክልል በማንነቱ ምክንያት አንድም ሰው ችግር ያልደረሰበት:: ትጋራይ አይደለም ኢትዮጵያዊያን የውጭ አገር ዜጎች በሰላም የሚኖሩባት ሰው አክባሪ ህዝብ ያላት ክልል ነች::ይህ ለወደፊቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል::
በመጨረሻም ውድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነትን ተላብሶ እንደሚጠናቀቅ ያለኝን ሙሉ እምነት እየገለጽኩ መልካም ቆይታ እንዲሆንላችሁና ቆይታችሁ የተሳካ፣ አስደሳች፣ አዝናኝና ትምህርት ሰጭ እንዲሆን እመኛለሁ::
ክብር ለሰማእታት 
አመሰግናለሁ

 

By admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Show Buttons
Hide Buttons